በተለያዩ የዲጂታል ካሜራዎች የመስራት እድሉን አግኝቼ ነበር። RED Scarlet, Canon DSLRs እንዲሁም Nikon DSLRs። እውነቱን ለመናገር DSLRsን ከRED ምስል ጋር ማነፃፀር ከባድ ነው፤ ሲጀመርም የዋጋ ክልላቸው በጣም ሰፊ ነው። ከዚህ ጀምሮ እስከ………………………………………ሩቅ ነው በጣም ይቅር!
ነገርግን DSLR ካሜራዎች ፕሮፌሽናል ምስሎችን አይሰጡም ማለት አይደለም። እንደውም አነስ ባለ ዋጋ እጅግ በጣም ውብ የሆኑ እና በማነኛውም ስራ ላይ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን ምስሎች ይሰጡናል። በዚህ ከተስማማን ሰለDSLR ማወቅ የሚገቡ ያልኳቸውን ካነበብኩት ላካፍላችሁ።
DSLR ካሜራዎች ምንድን ናችው?
ከDSLR ካሜራዎች በፊት የነበሩትን የፊልም ካሜራዎች በምናየበት ግዜ DSLR ቅርፁም ሆነ ይዘቱ እጅግ የተለየ ነው። ቅርፁ እና መጠኑ በሰፊው የፊልም መሀበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት እንዲያገኝ ቢያደርገውም ዋነኛው ምክንያት ግን እሱ አልነበረም። DSLR ካሜራዎች ዋጋቸው ከሌሎች የፊልም መቅረጫ ካሜራዎች እጅጉን የወረደ ሆኖ ሳለ ነገርግን የሚሰጡት ምስል ዋጋቸው ይበልጧቸው ከነበሩት አብዛኛዎቹ ካሜራዎች በልጦ ተገኝቷል። ጥቅማቸውም ከፎቶ ካሜራነት ብቻ መሆኑ ቀርቶ ወደ ቪዲዮ መቅረጫነትም አዘንብሏል።
DSLR ወይም Digital Single Lens Reflex የምንላቸው ካሜራዎች በዲጂታል ካሜራ ስር የሚመደቡ የካሜራ አይነቶች ሲሆኑ መሰታወትን በመጠቀም በሌንሱ በኩል የሚገባውን የብርሃን ምስል በቀላሉ በቪውፋይንደሩ በኩል ማየት እንድንችል የሚያደርጉ ናቸው።
እነዚህ ካሜራዎች የሚሰጡን ምስል HD ከመሆኑም በላይ በCF ካርዶች ወይንም SD ካርዶች ላይ የሚቀዳ ስለሆነ ተጠቃሚው በፈለገው እና በቀላሉ ሊጠቀምበት ይችላል።
DSLR ካሜራዎች ዋና አካላት
DSLR ካሜራዎች ውስብስብ ኤሌክትሮኒክ እና መካኒካል አካላት አሏቸው። ከነዚህ ውስጥ ግን ዋነኛውን ለማሳየት ሞክሪያለሁ።
- Lens_ሌንስ
- Reflex mirror_አንፀባራቂ መስታወት
- Shutter_የብርሃን በር
- Image sensor_የምስል ሴንሰር
- Matte focusing screen
- Condenser lens__ብርሃን ሰብሳቢ ስክሪን
- Pentaprism_አምስት ጎን ፕሪዝም
- Eyepiece/Viewfinder_የምስል መመልከቻ
DSLR ካሜራዎች እንዴት ነው የሚሰሩት?
ወደ ሌንሱ የሚገባው ብርሃን በ45 ዲግሪ የተጋደመውን አንፀባራቂ መስታወት ሲመታው የገባውን ብርሃን ወደ ባለ5 ጎኑ ፕሪዝም ይልከዋል። ይህ ፕሪዝም ደግሞ በቁመት የነበረውን ብርሃን ጎኖቹ ላይ በማገጫጨት ወደ አግድም ብርሃን ይለውጠዋል በዛን ግዜ በምስል መመልከቻው በኩል ምስሉ ይታያል። ባለካሜራው ፎቶ ለማንሳት ማንሻውን በሚጫንበት ግዜ የብርሃን በሩ ተከፍቶ የምስል ሴንሰሩ ብርሃን ይሰበስባል። ካሜራው ወደሴንሰሩ የገባውን ብርሃን የተለያዩ ውስብስብ የሆኑ ሰርኪውቶችን በመጠቀም ወደምስል ይቀይርልናል። በመጨረሻም ወደሚሞሪ ካርዳችን ይፅፍልናል። ይህ በሙሉ ሂደት የሚከናወነው ሰከንድ ባለሞላ ግዜ ውስጥ ነው። አንዳንድ DSLR ካሜራዎች ይህን ሂደት በሰከንድ እሰከ 11 ግዜ ያከናውኑታል።
እርሶስ ስለDSLR ካሜራዎች ምን የሚሉት አለ? በሚቀጥለው ፅሁፍስ ስለምን ማወቅ ይፈልጋሉ? ከታች ባለው አስተያየት መስጫ ላይ ይፃፉልኝ።
ሰማኝጌታ አይችሉህም፤ ኪያ
des ylal techemari negerochinm btnegren beteley sle lensochi ena tkmachew