የአንድ ተመልካች አይን የሚያየውን ምስል frame መወሰን ከፊልም ባለሙያው ከሚጠበቁ ብዙ ሃላፊነቶች አንዱ ነው። ተመልካቹ የፊልሙን አለም እና ቦታዊ አቀማመጡን እንዲሁም የሚመለከትበትን አቅጣጫ የተወሰነ እና የማያደናግር ለማረግ የ180 ዲግሪ ህግን እንጠቀማለን።

ህጎች ሁልጊዜ መሰበር የለባቸውም ማለት ትክክል አይደለም። ባለሙያው የራሱን ስነጥበባዊ እና ምስላዊ ገለፃን በፈለገው መንገድ ማሳየት ይችላል። ነገር ግን ተመልካቹ የፊልሙን ስነምድራዊ አቅጣጫ እና ቦታ አቀማመጥ በቀላሉ ለመረዳት ይችል ዘንድ የ180 ዲግሪ ህግን መጠቀም ታላቅ ቦታን ይይዛል።

የምስል አቅጣጫ(screen direction)የምንለው ለተመልቹ ግራ ወይንም ቀኝ ሆኖ የሚታየው አቅጣጫ ነው። ፊቱን ወደ ካሜራው የዞረ ተዋናይ ወደ ግራ ከሄደ በምስል አቅጣጫ ላይ ተቃራኒውን ቀኝ ይሄዳል ማለት ነው። 180 ዲግሪ ህግ የምንለው ይህን የምስል አቅጣጫ ከተለያዩ  አንግል እይታ የተቀረፁ ምስሎች በአንድ ላይ ኤዲት በምናረግበት ግዜ እንዲጠበቅ የሚረዳ ነው። ለምሳሌ አበበ እና አበበች ተጣልተው አበበች አበበን እያሯሯጠችው ነው። ከካሜራው እና ተመልካቹ አንፃር የምስል አቅጣጫ ወይንም የሚሮጡበት አቅጣጫ ወደ ቀኝ ቢሆን ካሜራውን በተቃራኒው አቅጣጫ ብናዞረው ወደ ቀኝ መሮጣችው ተገልብጦ ወደ ግራ ይሆናል። ስለዚህም የ180 ዲግሪ ህግ የሚለው በአበበ እን አበበች መሀል የማይታይ ቀጥታ ሀሣባዊ መስመር ቢኖር ይህንን መስመር ማለፍ የምስሉን አቅጣጫ ይገለብጠዋል ማለት ነው።

ሁለት በሚያወሩ ሰዎች መካከል የሚደረግ የምስል አቅጣጫ ተቃራኒ መሆን አለበት ያለበለዚያ ግን የሚያወሩ አይምስሉም። ለምሳሌ አበበ እና አበበች እየተጨቃጨቁ ነው።  አበበ የምስሉን ቀኝ ጠርዝ ይዞ ወደግራ እያየ የሚያወራ ከሆነ አበበች ደሞ በተቃራኒው ግራ ጠርዝ ላይ ሆና ወደቀኝ እያየች ማውራት ይኖርባታል። ሁለቱም ሰዎች በሚያወሩበት ግዜ የሚያዩት ወደ አንድ የተወሰነ አቅጣጫ መሆን ይኖርበታል። አበበ ወደግራ እያየ የሚያወራ ከሆነ ትዕይንቱ እስከሚያልቅ ወይንም ካሜራው እስከሚንቀሳቀስ ወደግራ ብቻ ማውራት ይኖርበታል።

 

የ180 ዲግሪ የተፈጠረው ተመልካቹ እንዳይደናገር እና የትዕይንቱን ስነምድራዊ አቅጣጫ እና የቦታ አቀማመጥ በቀላሉ እንዲረዳ ነው። ነገርግን የባለሙያው ምስላዊ ገለፃ እና ስነጥበባዊ እይታ ይወስነዋል።

ሰለ 180ዲግሪ ህግ ምን የሚሉት ወይም የሚጠይቁት አለ? በሚቀጥለው ፅሁፍስ ስለምን ማወቅ ይፈልጋሉ?ከታች ባለው አስተያየት መስጫ ላይ ይፃፉልኝ።